አስተዳደሩ በተቋም ደረጃ ላካሄደው የሪፎርም ስራ አስተዋፅዎ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ሰጠ፡፡

የግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 523/2015 አንቀጽ 6 (14) መሠረት አዲስ ተጠንቶ በጸደቀው የአስተዳደሩ መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሥራ መደብና ደረጃ ለተሰራው ስራ ከፍተኛ አስተዋፅዎ ላበረኩት የተለያዩ ተቋማትና ሰራተኞች፣የአስተዳደሩ የዋና መ/ቤትና የዲስትሪክት ኃላፊዎች የገንዘብና ሰርተፍኬት አበርክቷል፡፡
በዕውቅና አሰጣጥ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አባተ ምትኩ እንደተናገሩት የምናገለግለው በዕድሜ የገፉ የሀገር ባለውለታዎችን በመሆኑ በአዲስ አደረጃጀትና አስተሳሰብ አላማችንን ከግብ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ላበረከታችሁልን አስተዋፅዎ እናመስግናለን ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ የስራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ፍስኃፅዮን ቢያድግልኝ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአስተዳደሩ በተካሄደው መዋቅራዊ አደረጃጀትና ሪፎርም በርካታ ውጣ ውረዶችና የብዙ አካላት አበርክቶ እንደነበረበት ገልፀው በተጀመረው ለውጥ ውስጥ በመጓዝ በተሻለ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህ የዕውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር ላይ የመቀሌ ዲስትሪክት ከጦርነት ማግስት ወደ ስራ በመግባትና ለውጥ በማምጣት እንዲሁም የወልዲያ ቅ/ፅ/ቤት ሀላፊ የነበሩ ወ/ሮ ሰላማዊት ምትኩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት የቅ/ፅ/ቤቱ ንብረት እንዳይወድም በቤተክርስቲንና በቤቷ ደብቃ በማስቀመጥ ላከናወነችው ተግባር በልዩ ሁኔታ ዕውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡