መልስ 

በጡረታ አቅዱ ከተሸፈኑ የግል ድርጅቶችና ሠራተኞች የሚሰበሰበው የጡረታ መዋጮ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋሰትና አስተዳደር የጡረታ መዋጮ ገቢን ከመሰብሰብና ከማስፈፀም ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ስራዎች ለሌሎች አካላት ውክልና በመስጠት ማሰራት ይችላል ተብሎ በአዋጅ ቁጥር 715/2003 በአንቀጽ 11/11 ላይ ተደንግጓል፡፡

በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 587/2000 አንቀጽ 6 ከተሰጠው ሥልጣን መካከል ዘመናዊ የገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ ማድረግ በመሆኑ በአሁኑ ግዜ በመላ ሀገሪቱ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታክስና ቀረጥ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን በማቋቋምና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አደረጃጀት በመዘርጋት ለቁጥጥር አመቺ በሆነ መልኩ ለእያንዳንዱ ግብር ከፋይ በአሻራ ላይ የተመሰረተ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር (Tin number) በመስጠት ግብርና ታክስ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡በመሆኑም ባለስልጣኑ ካለው ተደራሽነትና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት አንፃር በአሰሪውና በሠራተኛው የሚከፈለው የጡረታ መዋጮ በባለስልጣኑ ( በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን) አማካኝነት ተሰብስቦ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ እንዲደረግ በመንግስት አቅጣጫ ሊያዝ ችሏል፡፡ ይህ አሰራርም በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል የሚሰሩ ተመሳሳይ ሥራዎችን አጣምሮ በመሥራት የሥራ ድግግሞሽን ( Duplication of work) እንደሚያስቀር ወጪን እንደሚቀንስና የጡረታ መዋጮ ገቢን ከምንጩ አሟጥጦ ለመሰብሰብ እንደሚችል ታምኖበታል፡፡ ስለዚህ በግል ድርጅቶችና ሠራተኞች የሚከፈለው የጡረታ መዋጮ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና የክልል የገቢ/የስራ ግብር ሠብሳቢ አካላት  በውክልና እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡

መልስ

  • የግል ድርጅቶች በግል ድርጅት ውስጥ ከአርባ አምስት ቀናት ላላነሰ ጊዜ ደመወዝ እየተከፈለው ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ስራ ለመስራት ከተቀጠረ ሰራተኛ የሰበሰበውን የጡረታ መዋጮ የራሱን ድርሻ ጨምሮ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና የክልል የገቢ/የስራ ግብር ሠብሳቢ አካላት ግብርና ታክስ በሚሰበስብበት ሥርዓት /መንገድ ደመወዝ ከተከፈለበት ወር ቀጥሎ ካለው ወር 30 ተከታታይ ቀናት ውስጥ የጡረታ መዋጮ ክፍያ ማሳወቂያ ቅጽ በሚጠይቀው መሠረት  በመሙላትና በሚመለከተው የስራ ሃለፊ ፊርማና  በድርጅቱ ማህተም በማረጋገጥ ከክፍያ ሰነዱ ጋር አባሪ አድርጎ የጡረታ መዋጮውን ገቢ ላደረገበት ግብር ሠብሳቢ መስሪያ ቤት በማስረከብ በሲፒኦ ወይም በጥሬ ገንዘብ ክፍያቸውን መፈጸም ይኖርባዋቸል፡፡

መልስ

 ከሰራተኛው መደበኛ የወር ደመወዝ በሰበሰበው የጡረታ መዋጮ ላይ የራሱን ድርሻ መዋጮ ጨምሮ በቀጣዩ ወር እስከ 30ኛው ቀን ድረስ ገቢ ያላደረገ የግል ድርጅት ከቀጣዩ ወር የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ  በባንክ የማስቀመጫ ወለድ መሰረት ወለድና 5 በመቶ ቅጣት በተጨማሪ ይከፍላል፡፡

  • ማንኛውም የግል ድርጅት ሠራተኛ በሚከፈለው መደበኛ የወር ደመወዝ ላይ ተመስርቶ የሚከፍለው የጡረታ መዋጮ 7 %  ነው፡፡
  • ማንኛውም የግል ድርጅት ለሠራተኛው በሚከፍለው መደበኛ የወር ደመወዝ ላይ ተመስርቶ የሚከፍለው የጡረታ መዋጮ 11% ነው፡፡

 መልስ

በአሁኑ ወቅት የማህበራዊ ዋስትና ዐቅዶችና አገልግሎቶች አስተዳደር ሲታሰብ በተለያዩ አዋጭ ምክንያቶች ተመራጭ እየሆነ የመጣው ጉዳይ የመረጃ ቴክኖሎጂን መጠቀም ነው፡፡ የመረጃ ቴክኖሎጂ የአጠቃቀምም ይሁን የልማቱ ደረጃ ከሚያስወጣው ወጪ አንፃር ፈታኝ ቢሆንም የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማምጣትና አስተማማኝ የፈንድ አስተዳዳር ስርዓትን ለመተግበር እጅግ ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡ ይህንን ግንዛቤ በመውሰድም ኤጀንሲው የጡረታ ምዝገባ ፤መዋጮ ገቢ መመዝገቢያ፤ የውሳኔና ክፍያ ሥርዓት/ሲስተም/ አሰርቶ እስካሁን እጅግ ሰፊ የሚባል የኔት ወርክ መሰረተ ልማት ግንባታ በሁሉም ፅ/ቤቶች ደረጃ የገነባ ሲሆን የየድርጅትና ሠራተኞች የጡረታ ማስረጃ ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተያዘ ሲሆን የጡረታ መዋጮ ምዝገባ መረጃ በማጥራትና ወቅታዊ በማድረግ  አዲስ በለማው መረጃ ሥርዓት/ሲስተም/ እየመዘገበ  ይገኛል፡፡ 

መልስ

የጡረታ መዋጮ የሚቆረጠው ለስራ ግብርና ለሌሎች ማናቸውም ጉዳይ (በህመም፣በዕዳ፣በቅጣት፣በትምህርትና በመሳሰሉት ምክንያቶች) ተቀናሽ የሚሆነው ሂሳብ ሳይነሳለት አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ በመደበኛ የሥራ ሠዓት ለሚሠጠው አገልግሎት ለሠራተኛው ከሚከፈለው መደበኛ ሙሉ የወር ደመወዝ ላይ ሲሆን  የትርፍ ሠዓት ክፍያን፣ልዩ ልዩ አበሎችን፣ጉርሻ ወይም ቦነስት፣ኮምሽን፣ማትጊያ፣ የአገልግለት ክፍያ እና የመሳሰሉ ጥቅማ ጥቅሞችን አይጨምርም፡፡

መልስ

ለግል ድርጅት ሠራተኛው ደመወዝ የሚከፈለው በቀን፣በሳምንት፣በአስራ አምስት ቀናት ወይም በቁርጥ ስራ ላይ በተመሰረተ ውጤት መሰረት ከሆነ የጡረታ መዋጮ የሚከፈለው በወሩ ውስጥ የተከፈለው መደበኛ ደመወዝ ተደምሮ ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ነው፡፡

መልስ

ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ከሆኑ የተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር የስራ ውል በማድረግ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ደመወዝ የሚያገኝ የግል ድርጅት ሠራተኛ በጡረታ ዐቅዱ የሚሸፈነው በአንዱና ሠራተኛው በመረጠው የግል ድርጅት ነው፡፡የግል ድርጅት ሠራተኛው በአንድ የግል ድርጅት በጡረታ ዐቅድ የተሸፈነና የጡረታ መዋጮ የሚከፍል ከሆነ በሌሎች በሚሰራባቸው የግል ድርጅቶች ከሚከፈለው ደመወዝ የጡረታ መዋጮ እንዳይቀነስበት በጡረታ ዐቅዱ ተሸፍኖ የጡረታ መዋጮ ከሚከፍልበት የግል ድርጅት ማረጋገጫ ደብዳቤ ማቅረብ አለበት፡፡ የግል ድርጅት ሠራተኛው ከሚሰራበት መስሪያ ቤት አንደኛው የመንግስት መስሪያ ቤት በመሆኑ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አቅድ የተሸፈነ ከሆነ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አቅድ አይሸፈንም፡፡

መልስ

በጡረታ ዐቅዱ በተሸፈነ የግል ድርጅትም ሆነ የግል ድርጅት ሠራተኛ ስም የተከፈለ የጡረታ መዋጮ ለሠራተኛውም ሆነ ለግል ድርጅቱ ተመላሽ አይደረግም፡፡

መልስ

  በመርህ ደረጃም ቢሆን በጣም አትራፊ የሆኑ መስኮች የዚያኑ ያህል የኪሳራ ስጋት ስላላቸው ትርፍን ብቻ መከተል አይቻልም፡፡ የአደራ ገንዘብ እንደመሆኑ የበለጠ መታየት ያለበት አስተማማኝነቱ ነው፡፡ ዛሬ ሥራ ላይ ያለው መዋጮ ከፋዩ የአቅዱ አባል ነገ ገንዘቡ ሳይጠፋ በእርግጠኝነቱ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃም ያለው ተሞክሮ አስተማማኝነቱ ላይ ያደላ ነው፡፡ በአጠቃላይ የማህበራዊ ዋስትና ኢንቨስትመንት የአደራ ገንዘብ በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ኢንቨስት መደረግ አለበት፡፡

መልስ

የአቅዱ አባላት በጡረታ ሲሰናበቱ የሚያገኙት የአገልግሎት አበል መጠን ከሠሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ተመጣጣኝ የሚባል ጥቅም የሚያስገኝ ነው፡፡ ለመጀመሪያ 10 ዓመት አገልግሎት የሦስት ዓመት (36 ወራት) አማካይ ደመወዝ 30% የሚታሰብ ሲሆን ከ10 ዓመት በላይ ለተፈጸመ ለእያንዳንዱ ዓመት 1.25% ተጨምሮ ይታሰባል፡፡ ሠራተኛው ወደ ጡረታ ሲሰናበት ከ36 ወራት አማካይ ጥቅል ደመወዝ (Gross Salary)እስከ  70% ድረስ ያገኛል፡፡ ሰራተኞች በሥራ ላይ እያሉ ከታክስ በኋላ ከሚከፈለው የተጣራ ተካፋይ ደመወዝ ጋር ደግሞ ገቢን የመተካት ምጣኔው (Replacement  rate) ረዥም አገልግሎት ላላቸው እንደ ደመወዛቸው መጠን ከ80 እስከ 100% ሊደርስይችላል፡፡

ምሳሌዎች፡

  • ሠራተኛው በጡረታ ሲሰናበት የ36 ወራት አማካይ ደመወዙ ብር 800 ቢሆንና አገልግሎቱ 42 ዓመት ቢሆን

የጥቅል አማካይ ደመወዙን 70% ማለትም ብር 560 የጡረታ አበል ያገኛል፡፡ በሥራ ላይ እያለ ከታክስ በኋላ የሚከፈለው የተጣራ ደመወዝ 671.50 ሲሆን ይህ የተጣራ ደመወዝ በጡረታ ሲሰናበት ከሚያገኘው የጡረታ አበል አንፃር የተተካለት (Replacement rate ) 83.39%ነው፡፡

  • ሠራተኛው በጡረታ ሲሰናበት የ36 ወራት አማካይ ደመወዝ ብር 5,000 ቢሆንና አገልግሎቱ 42 ዓመት

ቢሆን የጥቅል አማካይ ደመወዙን 70% ወይም ብር 3500 የጡረታ አበል ያገኛል፡፡ በሥራ ላይ እያለ ከታክስ በኋላ የሚከፈለው የተጣራ ደመወዝ ብር 3562.50 ነው፡፡ ይኽም ማለት በጡረታ አበል የሚያገኘው ጥቅም በሥራ ላይ እያለ ከሚከፈለው የተጣራ ደመወዝ 98.24% ይሆናል፡፡ ለወደፊቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ በቀጣይነት የእክል ዓይነቶችና ሽፋኑ ዕያደገ የሚሄድ ይሆናል፡፡

መልስ

በነበራቸው የጡረታ ዐቅድ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ ስለሚሸፈኑበት ወይም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ በቃለጉባዔ የተደገፈ ውሳኔያቸውን ለኤጀንሲው ያላሳወቁ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ከሃምሌ 1 ቀን 2003 ዓም ጀምሮ በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ይሸፈናሉ፡፡

መልስ

የፕሮቪደንት ፈንድ ወይም የጡረታ ዐቅድ ሽፋናቸውን በመተው በግል ድርጅት ሰራተኞች ጡረታ ዐቅድ ለመሸፈን የወሰኑ ሰራተኞች በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ለመሸፈን የወሰኑትን ውሳኔ ለመሻር አይችሉም፡፡

መልስ

የግል ድርጅት ሠራተኛው በነበረው የፕሮቪደንት ፈንድ ወይም የጡረታ ዐቅድ ሽፋን ለመቀጠል ወስኖ ከነበረበት የግል ድርጅት ጋር የነበረው የስራ ውል ከመቋረጡ ወይም እዚያው የግል ድርጅት ውስጥ አገልግሎ በጡረታ የሚገለል ከሆነ በጡረታ ከሚገለልበት ወር 3 አመት አስቀድሞ የተጠራቀመውን የፕሮቪደንት ወይም የጡረታ ዐቅድ ገንዘብ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ  ገቢ ማድረግ አለበት፡፡

መልስ

የግል ድርጅቱ የሚገኝበት አድራሻና ሠራተኛው የሚሰራበት አድራሻ የተለያየ ከሆነ የሠራተኛው የምዝገባ ማስረጃ የሚደራጀው የግል ድርጅቱ በሚገኝበት አድራሻ ነው፡፡ነገር ግን የግል ድርጅቱ ቅርንጫፍ ያለው ሆኖ ሰራተኛው ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የተቀጠረ ከሆነ የሠራተኛው የምዝገባ ማስረጃ የሚደራጀው በቅርንጫፉ አድራሻ ይሆናል፡፡

መልስ

የግል ድርጅት ሠራተኛው

  • በስራ ላይ ጉዳት ምክንያት በጡረታ የሚገለል ከሆነ በስራ ላይ ጉዳት ምክንያት ለማናቸውም ደመወዝ ለሚያስገኝ ስራ ብቁ አለመሆኑ በህክምና ቦርድ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ፣
  • በጤና ጉድለት ምክንያት በጡረታ የሚገለል ከሆነ በጤና ጉድለት ምክንያት ለማናቸውም ደመወዝ ለሚያስገኝ ስራ ብቁ አለመሆኑ በህክምና ቦርድ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ፤
  • ዕድሜ 60 በመድረሱ ምክንያት በጡረታ የሚገለል ከሆነ ዕድሜው 60 ከሞላበት ወር ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ፡፡

መልስ

ከአስር ዓመት በታች አገልግሎት ፈጽሞ የጡረታ  መውጫ እድሜው በመድረሱ ምክንያት በጡረታ የሚገለል የግል ድርጅት ሠራተኛ በጡረታ ከተገለለበት   ወር በፊት ይከፈለው የነበረው መደበኛ የወር ደመወዙ በ1.25 እና ባገለገለበት አመት ቁጥር ተባዝቶ  የአገልግሎት ዳረጎት ለአንድ ጊዜ ይከፈለዋል፡፡

መልስ

የግል ድርጅት ሠራተኛው የመንግስት ሠራተኛ፣ የህዝብ ተመራጭ፣የመንግስት ተሸዋሚ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባል፣የፖሊስ አባል፣የመንግስት የልማት ድርጅት ሠራተኛ፣ ከሃምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የመንግስት ፕሮጀክት ሠራተኛ በመሆን  የጡረታ መዋጮ እየከፈለ የፈጸመው አገልግሎት ባጠቃላይ በግል ድርጅት ውስጥ በጡረታ ዐቅዱ ተሸፍኖ ከፈጸመው አገልግሎት ጋር ተዳምሮ ለጡረታ አበል አወሳሰን ይታሰብለታል፡፡

መልስ

በፈጸመው ወንጀል 3 አመት እና ከዚያ በላይ  ጽኑ እስራት ቅጣት የተወሰነበት በመሆኑ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ መሰረት ጽኑ እስራቱ ከመወሰኑ አስቀደሞ በመንግስት መስሪ ቤት የፈጸመው አገልግሎት ለጡረታ አበል አወሳሰን ያልተያዘለት የግል ድርጅት ሠራተኛ ይህ አገልግሎት ከሃምሌ 1 ቀን 2007 ዓም ጀምሮ   ለጡረታ አበል አወሳሰን ይታሰብለታል፡፡

መልስ

በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ወይም በመንግስት ሠራተኞቸ ጡረታ አዋጅ መሠረት መጦሪያ ዕድሜ60 ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ የአገልግሎት ጡረታ አበል የተወሰነለት ባለመብት እንደገና በመቀጠር የፈጸመው አገልግሎት ከቀድሞ አገልግሎቱ ጋር ተደምሮ አበሉ ተሻሽሎ የሚከፈለው መጦሪያ ዕድሜው 60 ላይ ከደረሰበት ቀጥሎ ካለው ወር የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ሆኖም እንደገና የታሰበው አበል ከቀድሞው አበል ያነሰ ከሆነ የቀድሞውን አበል የማግኘት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ሥራ በመመለስ ለፈጸመው አገልግሎት የሚከፈለው አበል ወይም የጡረታ መዋጮ ተመላሽ አይኖርም፡፡

መልስ

የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሌለው የግል ድርጅት ሰራተኞች በገል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ይመዘገባል፣ሲመዘገብም ጊዜያዊ የማህበራዊ ዋስትና መለያ ቁጥር በኤጀንሲው ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም የግል ድርጅቱ ወይም የግል ድርጅት ሠራተኛው  ከግብር ሰብሳቢው አካል የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እንዲሰጠው በመጠየቅ ሲሰጠው ለኤጀንሲው በማቅረብ ጊዜያዊ የማህበራዊ ዋስትና መለያ ቁጥሩ በግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩ እንዲለወጥ ማድረግ አለበት::