በአስተዳደሩ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃግብር ተካሄደ፡፡

የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለአቅመ ደካሞችና የደመወዝ ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች እንዲሁም ከተቋሙ ጋር በጋራ(በአውት ሶርስ) ለሚሰሩ ሠራተኞች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር አካሄደ፡፡በማዕድ ማጋራቱ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አባተ ምትኩ እርስ በርስ መተጋገዝና መደጋገፍ ኢትዮጵያዊ የቆየ እሴት በመሆኑ አስተዳደሩም አብሮነትን ለማሳየት ዛሬ የገና በዓልን አስመልክቶ የማዕድ ማጋራት ተግባር ማከናወኑን ገልፀዋል፡፡አነስተኛ ገቢ ካላቸው የአስተዳደሩ ሠራተኞች ባሻገር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ለሚኖሩ ከ100 በላይ አቅመ-ደካሞችም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ የማጋራት ተግባር መከናወኑን የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጠቅሰው በቀጣይም አስተዳደሩ የበጎነትና የሰብዓዊነት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በቦሌ ክ/ከተማ የወረዳ 05 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ እየሩስ ባስተላለፉት መልዕክት አስተዳደሩ የገና በዓልን አስመልክቶ በወረዳው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ላደረገው የበጎነትና ሰብዓዊነት ተግባር ያመሰገኑ ሲሆን ፤ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት የተደረገላቸው ገቢያቸው አነስተኛ የሆነ የተቋሙ ሰራተኞችም ለተደረገላቸው ተግባር አመስግነዋል፡፡