የማኅበራዊ ዋስትና/social insurance/ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለዉ በጀርመን ሀገር እ.ኤ.አ. ከ1883-1889 ነው፡፡ምክንያቶቹም የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ በሠራተኞች ላይ የጉዳት መበራከት፣ የተፈጠረዉ ርካሽ ጉልበት ደመወዝን ዝቅተኛ በማድረጉ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ዝቅተኛ ደመወዝ መከፈሉ ናቸው፤ሠራተኛው ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው ደመወዝ ቀንሶ ቁጠባ መቆጠብ አልቻለም፡፡ በልዩ ልዩ እክሎች ምክንያት ሠራተኛዉ መደበኛ ሥራዉን ማከናወን ሳይችል ሲቀር ከሥራ መፈናቀልና የገቢ መቋረጥ ይደርስበታል፡፡ በተለይ በዕድሜ ምክንያት ሥራ የሚለቁ ሰዎች መተዳደሪያ እያጡ መምጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ፡፡
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር እንደመሆኗ ማዕከላዊ መንግስት ሲመሠረት በሥርዓቱ ውስጥ ባሉ ግዛቶች ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወታደሮችና ሠራተኞች ተቀጥረው ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት እነዚህ ሠራተኞችና ወታደሮች የዕድሜ መግፋት አይቀርምና ያረጃሉ፣ በሥራ ላይ እያሉም ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ስለሆነም የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎትን መዘርጋትና መተግበር ቀዳሚ ተግባር መሆኑ ታመነበት፡፡
የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት የራሱ ቅርፅና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው እንደዚሁም በጥናት ላይ እንዲመሠረት ለማድረግ በ1949 ዓ/ም በአገር አቀፍ ደረጃ ጥናት አድራጊ ኮሚቴ ተደራጅቶ ጥናት ማካሄድ ጀመረ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም በ1950 ዓ/ም በህግ ደረጃ የጡረታ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመንግስትና በጊዜው የነበሩ በጣት የሚቆጠሩ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ አገልግሎት የሚያገኙበትን ጥናት አጥንቶ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ 1953 ዓ.ም ላይ መፈንቅለ መንግስት ተካሄዶ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የመንግስት ደጋፊዎችና ተቃዋሚ ወታደሮች አካላቸው ተጎዳ፤ ህይወታቸው አለፈ፤ ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊ ቀውስ ተፈጠረ፤የወታደሮች አካል መጎዳት፣ ህይወት ማለፍና የመንግስት መሥሪያ ቤቶችና ጥቂት ፋብሪካዎች መቋቋማቸው በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋንን የሚመለከት አዋጅ መውጣት አስገዳጅ መነሻዎቹ ሆኑ፡፡
በዚህም የጡረታ አዋጅ ያኔ
‹‹ዲክሪ
›› ነው የሚባለው ቁጥር 46/53 በአገር አቀፉ ደረጃ የህግ ማዕቀፍ ሆኖ ፀድቆ በ1955 ዓ.ም የመዋጮ ህጎችን እንደዚሁም በ1967 ዓ.ም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን እንዲያቅፍ ተደርጎና ማሻሻያዎችን አካቶ በድጋሚ ወጣ፡፡
የጡረታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎቱን ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች የሚስፋፋበትን በ1975 ዓ.ም እንዲያጠና በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በወቅቱ አገሪቱ ትከተለው ከነበረው ርዕዮተ-አለም አኳያ የግል ድርጅቶች ስላልተስፋፉ በጥናታቸው ውስጥ አስር እና ከዚያ በላይ ሠራተኞችን የሚያሠሩ የግል ድርጅቶችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት በጡረታ አገልግሎት የሚታቀፉበት ሁኔታ አጥንተው አቅርበው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት የአገር ውስጥና የውጪ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የማኅበራዊ ዋስትና አስፈላጊነቱንና ሽፋኑን በሚመለከት ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
በመቀጠልምየኢፊዲሪ ህገ-መንግስትን ድንጋጌዎች እና የዓለም ሥራ ድርጅቶች ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ ረቂቅ አዋጁን በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ማለትም፡-ከአሠሪዎች ፊዴሬሽን እና ከኢሠማኮ ተወካዮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ በረቂቅ አዋጁ ላይ ማሻሻያዎች እየተደረጉ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡
እንደሚታወሰው በአገሪቱ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት ሽፋን የነበራቸዉ የመንግሥት ሲቪል ሠራተኞች፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ብቻ ነበሩ፡፡ ይህን ዉስን የነበረዉን ሽፋን ለማስፋት መንግሥት በግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችም የጡረታ ዐቅዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በ2003 ዓ/ም ውሳኔ በማሳለፍ አዋጅ ቁጥር 715/2003 እንዲወጣ ተደረገ፡፡ በዚሁ መሠረት የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁ.202/2003 ተቋቋመ፣፡
ኤጀንሲው እንደተቋቋመ በርካታ ሥራዎቹን በመሥራት በየግል ድርጅቶቹ በመሄድ ምዝገባ መመዝገብና መዋጮ መሰብሰብ ቀጠለ፡፡ በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችንና ክፍተቶችን በመለየት እንደገና 2007 ዓ/ም የተሻሻለ አዋጅ ቁጥር 908/2007 እንዲወጣ ተደረገ፡፡
በዚህም የግል ድርጅት ሠራተኛ በዕድሜ መግፋት፣ በጤና ጉድለት ወይም በሥራ ላይ በሚደርስ የአካል ጉዳት ምክንያት ሥራዉን ማቋረጥ ሲገደድ ገቢዉ ሳይቋረጥ ኑሮዉን መምራት የሚያስችል ዘላቂ የጡረታ አበል እንዲያገኝ ተደርጓል፤ከዚህም በላይ ሠራተኛዉ በሞት ሲለይ ለተተኪዎች በዘላቂነትና በዳረጎት መልክ ጥቅሙን ማስተላለፍ ተችሏል፡፡
ኤጀንሲውም የተሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ከፍተኛ የጡረታ ፈንድ ገንዘብ የሚያስተዳድር ተቋም እየሆነ ከመምጣቱም በላይ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያመነጨው የፋይናንስ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በመሆኑም ይህንን ገንዘብ በአግባቡ ለማስተዳደርና በኢንቨስትመንት መስኮች በመግባት ፈንዱን ለማዳበር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው የአዋጅ ለውጥ አስፈልጓል፡፡
በዚሁ መሰረት ” የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ” በሚል አዲስ የጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 በህ/ተ/ም/ቤት ጸድቆ በማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 523/2015 በሚኒስትሮች ም/ቤት እንደገና ተቋቁሞ በተግባራዊ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ስለሆነም “የጡረታ አዋጅ ቁ.1268/2014፡-
- የማኅበራዊ ዋስትናን ሥርዓት በማስፋፋት ደረጃ በደረጃ ለዜጎች እንዲዳረስ በማድረግ ከሀገሪቱ ማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲ አንዱ አካል በመሆኑ፤
- የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድን እና ፈንድን በማሻሻልና በማጠናከር ዘላቂነትና አስተማማኝነቱን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
- በሀገሪቱ እየታየ ካለዉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዋስትና ዕድገት ጋር የተጣጣመና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትና አሠራሩን ማዘመን ስለሚገባ፤
- እንዲሁም ለማኅበራዊ ፍትህ፣ ለኢንዱስትሪ ሠላም፣ ለድህነት ቅነሳና ለልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረዉ ስለታመነ የታወጀ ሲሆን፤
የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደርም አሠሪ ድርጅቶችንና በግል ድርጅቱ አንድና ከአንድ በላይ ተቀጥረው የሚሠሩ እንዲሁም ለ45 ቀናትና በላይ ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላቸውን ሠራተኞችን በመመዝገብ፣ የባለመብቶችን አበል በመወሰንና በመክፈል አገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ ሥር ነቀል ሪፎርም በማካሄድ የሚመዘግባቸው ድርጅቶችና ሠራተኞችን እንዲሁም የሚሰበሰበውን የመዋጮ ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ መጥቷል፡፡
ለአብነት፡-
|
በ2014 በጀት ዓመት |
በ2015 በጀት ዓመት |
በ2016 በጀት ዓመት |
በ2017 በጀት ዓመት |
ምርመራ |
ድርጅት |
10,159 |
13,433 |
18,747 |
25,664 |
|
ሠራተኛ |
126,213 |
163,251 |
166,334 |
210,493 |
|
መዋጮ |
15,364,542,656 |
20,776,969,150 |
28,735,846,870 |
40,792,783,220 |
|
የግል ድርጅቶችንና ሠራተኞችን በመመዝገብ እና የጡረታ መዋጮ በመሰብሰብ በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም አስተዳደሩ እስካሁን የሚሠራበትን የማኑዋል አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመቀየር ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም በ2018 ግማሽ ዓመት ላይ ይገባደዳል ተብሎ ይታሰባል፤የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚዎች ቀልጣፋና የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት በመትጋት ላይ ይገኛል፡፡
አመሰግናለሁ !
አባተ ምትኩ ዋቀዮ
ዋና ሥራ አስፈፃሚ