የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ማጠቃለያ ሪፖርት

የዐቅድ አባልነት ምዝገባ፡- የጡረታ ሽፋንን ለማሳደግ ከሚሠሩት ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የግል ድርጅቶችንና ሠራተኞቻቸውን በመመዝገብ የዐቅድ አባልነት ካርድ መስጠት አንዱ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 7,830 ድርጅቶችን እና 65,424 ሠራተኞችን ለመመዝገብ ታቅዶ 8,944 ድርጅቶችን እና 62,217 ሠራተኞችን መመዝገብ ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙ በድርጅት ምዝገባ 114 በመቶ ሲሆን በሠራተኛ ምዝገባ 95 በመቶ ነው፡፡ በሩብ ዓመቱ ለ 8,144 ድርጅቶችና ለ 51,110 ሠራተኞች የዐቅድ አባልነት ካርድ ተሰጥቷል፡፡

የጡረታ ፈንዱን ማዳበር፡- የጡረታ መዋጮ አሟጦ መሰብሰብ አንዱ የአስተዳደሩ አብይ ተግባር ነዉ፡፡ በዚህ መሠረት በሩብ ዓመቱ ብር 13,514,986,379 የጡረታ መዋጮ ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 12,510,221,585 ተሰብስቧል፡፡ አፈፃፀሙም 93 በመቶ ነው፡፡

የድርጅቶች የጡረታ መዋጮ ኦዲት፡- ተመዝግበው የጡረታ ዐቅድ አባል የሆኑ ድርጅቶች በትክክልና ለሁሉም ሠራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ እየከፈሉ ስለመሆናቸው የኦዲት ሥራ የሚከናወንበት ሲሆን በሩብ ዓመቱ 4,546 ድርጅቶችን ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ 4,024 ድርጅቶችን ኦዲት ማድረግ ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙ ከዕቅድ ጋር ሲነፃፀር 89 በመቶ ነው፡፡

በሕግ አስገዳጅነት፡- አስተዳደሩ ስለአሠራሩና ስለማህበራዊ ዋስትና አፈፃፀም ግንዛቤ ከማስረፅ ሥራ በተጓዳኝ የሕግ አግባብን በመከተል የጡረታ መዋጮ ገቢ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት የሚጠበቅባቸውን የጡረታ መዋጮ ባልከፈሉ የግል ድርጅቶች ዉዝፍ የጡረታ መዋጮ ከባንክ ሂሳብ ተቀንሶ ለፈንዱ አካዉንት ገቢ እንዲሆን ብር 250,000,000 ተጠይቆ ብር 253,464,397 (101 በመቶ) ወደ ጡረታ ፈንዱ ገቢ ተደርጓል፡፡

ኢንቨስትመንት፡- የጡረታ ፈንዱን ኢንቨስትመንት ላይ በማዋልና ትርፍ በማግኘት አስተማማኝነቱንና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ሌላው የአስተዳደሩ ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ በዚህ መሰረት ብር 183,571,377,699 ኢንቨስትመንት ላይ ያለ ሲሆን በሩብ ዓመቱ ብር 4,450,000,000 ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ ብር 4,965,758,095 ትርፍ ተገኝቷል፡፡ አፈጻጸሙ 112 በመቶ ነው፡፡

ትርፉ የተገኘባቸው የኢንቨስትመንት መስኮችም፡ ከግምጃ ቤት ሰነድ ብር 1,865,624,318፤ የግምጃ ቤት ቦንድ ብር 2,748,959,192፤ የኢ/ል/ባንክ ቦንድ ብር 105,410,959፤ የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ብር 227,479,452 እና የአበል ክፍያ ተቀማጭ ብር 18,284,174 ናቸዉ።

የጡረታ አበል ውሳኔ፡- በሩብ ዓመቱ 1,897(1,304 ወንድ እና 593 ሴት) ባለመብቶች የአበል ውሳኔ እና ክፍያ ትእዛዝ ተዘጋጅቶ ክፍያውን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡