አዲስ አበባ፡ መስከረም 3/2017 ዓ.ም፡ የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር እና የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በጋራ ለሚያስለሙት ሲስተም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጋር የሶስትዮሽ የሥራ ውል ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነቱ ላይ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትግስት ሃሚድ፣ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አባተ ምትኩ እና የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን በቀለ ተቋሞቻቸውን በመወከል የስራ ዉል ስምምነቱን ፈርመዋል።
የሶስትዮሽ ስምምነቱ ዌብ ላይ መሰረቱን ያደረግ የተቀናጀ ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ሲሆን ስራዉ በውስጡ-7 ንዑስ ሲስተሞች የያዘ ነዉ።
ትግበራዉ ሲጠናቀቅ የጡረታ ምዝገባን፣ የጡረታ መዋጮ ክፍያን፣ የጡረታ ተጠቃሚነትን እና ሌሎች ስርዓቶችን በማቀናጀት እና በቴክኖሎጂ በማዘመን ሥራን የሚያቀላጥፍ ነዉ።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሥራውን በባለቤትነት በመውሰድ በሚፈለገው ጥራትና ከተቀመጠቀው የጊዜ ሰሌዳ ባጠረ ጨርሶ እንደሚያስረክብ ጠቁመዋል።
የስራውይ በጊዜ መጠናቀቅ ከተቋማቱ ባሻገር ለዜጎች የሚኖረዉ ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ በትኩረት እንደሚሠራ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አባተ ምትኩ በበኩላቸው ይህ ፕሮጀክት በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ኢመደአ በባለቤትነት ሥራውን በሚፈለገው ጥራት እና ጊዜ እንደመሠራው እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጥላሁን በቀለም ሁለቱን በስምምነቱ ላይሃሳባቸዉ የሰነዘሩ ሲሆን ተቋማት ለማቀናጀት እና በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከሶስት ዓመት በፊት የሪፎርም ሥራው መጀመሩን ጠቁመው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የጡረተኞች ክፍያን የማሰባሰብና ገቢን የማሳደግ ሥራው በተሸለ ማቀላጠፍ የሚያስችል ጥልቅ የአሠራር ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡