የአስተዳደሩ ሠራተኞች የመቄዶኒያ አረጋዊያን ማዕከልን ጎበኙ

በጉብኝቱ ወቅት የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባተ ምትኩ በቦታው በመገኘት ባደረጉት ንግግር “ነገ የሁላችንም ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፤ ዛሬ እዚህ ቦታ መጥተን የጎበኘናቸው አረጋዊያን ትናንት ሀገርን ተሸክመው እዚህ ያደረሱ ባለውለታዎች ናቸው፡፡ በጆሯችን ከምንሰማውና ከሚነገረን በላይ በቦታው መጥተን በዓይናችን ማየታችን መቄዶኒያን ዘውትር እንድናስብና የአቅማችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይረዳናል” ብለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለው “አስራ ሁለት ዓመት ሳይቋረጥ በተለይም በቀን አንድ ሚሊዮን ብር እያወጡ መመገብና መንከባከብ የሚታሰብ አይደለም፤ ይህ ኃላፊነት እኛ ላይ ወድቆ ቢሆን በጣም በጣም ያስጨንቃል፡፡ ዶ/ር ቢኒያምን ግን ፈጣሪ እየረዳው እዚህ ደርሷል፤ እኛም በግል ከምናደርገው በተጨማሪ እንደ ተቋም በመላው ሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ጽ/ቤቶቻችን ያለ ሠራተኛ በአቅሙ ልክ ማዕከሉን ሊያግዝ ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከሉ መስራች የክብር ዶ/ር ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው “በአካል መጥታችሁ ስለጎበኛችሁን ደስ ብሎናል፤ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን” ካሉ በኋላ “አረጋዊያን ከምንም በላይ የእናንተን ፍቅር እና ድጋፍ ይፈልጋሉ፤ተቋሙን በገንዘባችሁ፣በእውቀታችሁ፣ እና በጉልበታችሁ እንድታግዙና ሌሎችንም ለድጋፍ እንድትቀሰቅሱልን እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡

ከጉብኝቱ መልስ በዋናው መ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገ ውይይት የተቋሙ ሠራተኞች በቦታው ሄደው በመጎብኘታቸው ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በሙሉ ፍቃደኝነት ከወር ደመ-ወዛቸው በዘላቂነት እየተቆረጠ ለማዕከሉ እንዲሰጥላቸው መወሰናቸውን ገልጻዋል፡፡

አስተዳደሩ ከዚህ በፊት በገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር እና በአይነት እንዲሁም ያገለገሉ የቢሮ ቁሳቁሶችን መርዳቱን ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡

Leave Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *